በልዑል እግዚአብሔር ቸርነት ደብራችን ከተመሠረተች ጀምሮ ላለፉት አሥር አመታት አገልግሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች። የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሁሌም በፈተና ውስጥ ነው። በተለይ በውጭው አለም ለሚገኙ አጥቢያዎች ሁሉ ማለት ይቻላል አገልግሎታቸውን የሚሰጡበት በቋሚነት የሚገለገሉበት ሕንጻ አለመኖር አንዱ ትልቁ ፈተና ነው።

ከደብሩ ምሥረታ ጀምሮ በኪራይ ስንገለገልበት የቆየው "ተፍነል ፓርክ" አካባቢ የሚገኘው የቅ. ጊዮርጊስ የአንገሊካን ቤተ ክርስቲያን እ.ኤ.አ. 2013 ዓ.ም. ሕንጻውን ለእድሳት እንደሚፈልጉት በመግለጽ ሌላ ቦታ እንድንፈልግ ጠየቁን። በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ፣ በወቅቱ በነበሩ ካህናት እና ምእመናን ፍለጋ እና በሰ/ምዕራብ አውሮፓ ሀ/ስብከት ትብብር ሌላ ሕንጻ በኪራይ ለማግኘት በቃን። በአሁኑ ወቅት እየተገለገልንበት ያለውን ይኼንኑ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለቅቀን እንድንወጣ ተጠይቀናል።

መፍትሔው ምንድን ነው?

ጊዜያዊ

አገልግሎታችን ላይ ምንም ዓይነት መስተጓጎል እንዳያጋጥመን፣ ቅዱሳት ታቦታቱ፣ ንዋየ ቅድሳቱ ማረፊያ እንዳያጡ ከጸሎት ጋር ሁላችንም ተግተን ሌላ መገልገያ ቦታ ማግኘት ይኖርብናል። እርስዎስ ምን ምን አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው?

ሊጠቁሙት የሚፈልጉት የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ፣ አዳራሽም ይሁን ሌላ ለቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት የሚስማማ ሕንጻ ካለ እዚህ ገጽ ላይ በመሄድ ጥቆማዎን/መረጃውን ማካፈል ይችላሉ።

ዘለቄታዊ መፍትሔ

ዘላቂው መፍትሔ ቋሚ የሆነ ሕንጻ መያዝ ነው።

በአውሮፓ የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን አንዱ ችግር የአገልግሎት ቦታ ነው። በግዢም ይሁን በሌላ መልኩ የራሳቸው የሆነ ቋሚ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ያላቸው በጣም ጥቂቶች ናቸው። እኛም በስንፍናም ይሁን በሌላ ምክንያት የሚጠበቅብንን ያህል ተግተን ባለመሥራታችን፣ አብዛኛው ምእመን አሥራቱን ሊያወጣ ቀርቶ መደበኛ የሰ/ጉባኤ አባልነት ክፍያውን እንኳን በትክክል መፈጸም አለመቻሉ ለዚህ አስተዋጽኦ አድርጓል። በሌላ መልኩ የሚሸጡ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎች እንኳን ቢኖሩ ለግዢ የሚፈልጓቸው የእምነት ተቋማት ብዛት፣ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ውጪ ለሙዚየምነት፣ የገበያ አዳራሽ፣ ሕንጻውን ቀይሮ መኖሪያ ቤቶች ለመሥራት ... የሚፈልጋቸውም መብዛቱ ውድድሩን ከፍተኛ ያደርገዋል። ልጆቻችንን እምነት ከምግባር በማስተማሪያ ወቅት እኛ ገና ንዋየ ቅድሳቶቻችንን ይዘን ከሕንጻ ሕንጻ እንንከራተታለን። አበው ሲተርቱ 《የሰው ወርቅ አያደምቅ》 ይላሉ። ዛሬ ፈልገን በኪራይ የምንገባበት ሕንጻ ነገ ከነገ ወዲያ ደግሞ ሌላ 《ልቀቁ》 ሳይመጣብን መፍትሔው ቋሚ ቦታ ማዘጋጀት ብቻ ነው።

ከባንክ ባገኘነው /preliminary estimate/ መሠረት የምንገዛውን ሕንጻ 40% ያህል ቅድሚያ ክፍያ መፈጸም እስከቻልን ድረስ የደብራችን የገቢ መጠን በማየት ከ1.75-2 ሚሊዮን ፓውንድ ድረስ ሊያበድሩን እንደሚችሉ ተረድተናል። (የመጨረሻው ቁጥር በምንገዛው ሕንጻ ዋጋ፣ ቅድሚያ መክፈል በምንችለው መጠን እና ባንኩ እኛ ላይ በሚኖረው እምነት የሚወሰን ይሆናል)

አሁን ለንደን ላይ ያለውን ዋጋ ስናጤን ቢያንስ £2,000,000 ያስፈልገናል። የዚህ 30% (ቋሚ ገቢያችን እና የመሳሰሉት መስፈርቶች ተሻሽለው ባንኩን ማሳመን ከቻለ) ደግሞ £600,000 ይሆናል።አለበለዚያ በ40% ቅድሚያ ክፍያ ከሆነ ግን አጠቃላይ የሚኖረን አቅም £1,500,000 ብቻ ይሆናል ማለት ነው። ይኼ ደግሞ በጣም ትንሽ፣ ወይም ደግሞ ከመሃል ከተማ ራቅ ያለ ቦታ ለመሄድ ያስገድደናል።

እስከ አሁን የተሰበሰበ
£600,000 £450,000

ባንኩ ሊያበድረን የሚችለውን መጠን ከሚወስኑ ነገሮች አንዱ መፈጸም የምንችለው ቅድሚያ ክፍያ ነው። ይኼ ቁጥር እንዲጨምር የበኩልዎን አስተዋጽኦ አድርገዋል? ካላደረጉ ዛሬ ነገ ሳይሉ ካሉት አማራጮች የሚቀልዎትን በመጠቀም ይጀምሩ። ያስታውሱ፦ ለሕንጻ ግዢ ራሱን የቻለ ዝግ የባንክ ሒሳብ ያለው ሲሆን ለእለት ከእለት አገልግሎት (ያለንበትን ሕንጻ ኪራይ፣ መብራት እና ጋዝ ጨምሮ) የምንጠቀመው ከመደበኛ የሰ/ጉባኤ አባልነት፣ ከሙዳየ ምጽዋት፣ ከልዩ ልዩ የጽ/ቤት ክፍያዎች እና ከመሳሰሉት የሚሰበሰበውን ገንዘብ ነው።

ሌላኛው ባንኩ ሊያበድረን የሚችለውን መጠን ከሚወስኑ ነገሮች አንዱ የመደበኛ ገቢያችን መጠን ነው። መደበኛ ገቢያችንን ቋሚ እና አስቀድሞ መገመት የሚቻል /predictable and reliable/ እንዲሆን Direct Debit ክፍያ እያዘጋጀን ሲሆን ዝርዝሩን በቅርቡ እዚሁ ድረ ገጻችን ላይ እናቀርባለን። እስከዚያው ሰ/ጉባኤ ጽ/ቤት በመምጣት፣ በስተግራ በሚገኙት አማራጮች በመጠቀም ... ወዘተ የድርሻዎን እንዲወጡ እና የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ መንፈሳዊ ግብዣችንን እናቀርባለን።

ልዑል እግዚአብሔር ንዋየ ቅድሳቱ በሚገባቸው ክብር የሚቀመጡበትን፣ አገልግሎታችን በድንጋይ ከተሰራው የመጀመሪያው ሕንጻ ግዢ አልፎ ወደ ሌላኛው ሕንጻ/የእኛ ሥጋ/ ሥራ /1 ቆሮ 6፥19/ የሚሸጋገርበት ቀን ቅርብ ያድርግልን።

የተጠቃሚ መግቢያ