የአብርሃሙ ሥላሴ

በሊቀ ጉባኤ ጥበበ ሥላሴ አሰፋ

ሐምሌ 7 ቀን እግዚአብሔር በአንድነት፣ ሥላሴ በሦስትነት ለአብርሃም በቤቱ የተገለፁበት፣ በእንግድነት ተገኝተው ቤቱን የባረኩለት፣ በበጎ ህሊናው በትሁት ስብዕናው ያቀረበላቸውን ማዕድ የባረኩለትና ለሣራም ማህፀኗን ባርከው በስተእርጅና ይስሐቅን እንደምትወልድ ያበሰሩት ዕለት ነው።

አንድነትን ሦስትነትን የምንማርበት ትምህርት ቢኖር ዋነኛው እግዚአብሔር በአብርሃም ቤት የተገለፀውን መገለፅ መመልከትና መመርመር በቂ ነው። ታሪኩን በሙሉ በቅዱስ መጽሐፍ እናገኘዋለን ኦሪ. ዘፍ 18-1-33 

አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም፣ በግብር፣ በአካል ሦስት፤ በባህርይ፣ በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ አንድ ናቸው። ለዘመናቸው በዚህ ጊዜ ተገኙ በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አንልም ፊተኛና ኋለኛ፣ መጀመርያና መጨረሻ፣ አልፋና ኦሜጋ ናቸው። ራዕ 22፥13

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ አባታችን አብርሃም የእምነት፣ የደግነት፣ የታዛዥነትና የፍፁምነት ምሣሌ ነው።

የአብርሃም እምነት የእግዚአብሔርን ቃል ተቀብሎ ያለ ጥርጥር ወደ ታዘዘው ቦታ መሄዱ እግዚአብሔርን በማመን ከሚያውቃቸው ወገኖቹ  ካደገበት መንደርና ከኖረበት ሃገር ወደማያውቀው ሃገር ህዝብና መንደር መጓዙ እምነቱን ፍፁም ያደርገዋል።

“እግዚአብሔርም አለው ከሀገርህ ከዘመዶችህ ከአባትህ ቤት ተለይተህ እኔ ወደምልክህ ምድር ውጣ።” ዘፍ 12፥1

ምስጢር፦ በእግዚአብሔር ስናምን በምድር ቤት፣ ወገን፣ ሀገር ሃላፊ ቀሪና ጠፊ በመሆናቸው የማይጠፋ ሀገር የማይለወጥ አባት የዘለዓለም ቤት ምንግሥተ ሰማያት እንዳለን የሚያጠይቅ መልዕክት ነው።

የአብርሃም ደግነት፦ ያለውን አካፍሎ፣ መንገደኞችን ተቀብሎ በድንኳኑ አስተናግዶ የሚሸኝ የደግነት አባት ነው። ይህን ደግነቱን ያየ ሰይጣን ቀንቶበት እንግዳን ቢያስቀርበት እግዚአብሔር ቤቱን ሊባርክ መሥዋዕቱን ሊቀበል በሰው ተመስሎ ወደ ቤቱ መጣ።

ዘፍ፦ 18፥1 “በቀትርም ጊዜ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለፀለት አይኑንም አነሣና እነንያ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፤ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ ወደ ምድርም ሰገደ እንዲህም አለ “አቤቱ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ” አለ። አንድነቱን መንፈስ ቅዱስ ገልፆለት “ባሪያህን አትለፈኝ” አለ።

ሦስትነቱን ደግሞ ሲገልፅለት

“ጥቂት ውሃ ይምጣላችሁ እግራችሁን ታጠቡ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ ቁራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ ልባችሁንም ደግፉ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መጥታችኋልና”

በማለት የሥላሴን ጌትነት የእርሱም አገልጋይነት ደግነትና አምልኮት ያስተምረናል። ሌላው ከአብርሃም የምንማረው ታዛዥነትና  ፍፁምነት ነው።

የአብርሃም መገለጫውና መታወቂያው ታዛዥነትና ፍፁምነት ነው። ሰው እግዚአብሔርን ካመለከ ሊሆን የሚገባው እንደ አብርሃም ነው። እግዚአብሔርም ይህን ደገኛ ባህርዩን ተመልክቶ “እኔ የአብርሃም አምላክ ነኝ“ ብሎ መስክሮለታል። አብርሃም በ 99 ዓመቱ ያገኘውን ልጁን ይስሐቅን ለመስዋዕት እንዲያቀርብ በተጠየቀ ጊዜ ሳይሳሳ እና ሳያመነታ ልጁን ለመስዋዕት አቀረበው።

ዘፍ 22፥1 “አብርሃም ሆይ አለ እግዚአብሔር አብርሃምም እነሆኝ አለሁ አለ” የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞርያ ምድር ሂድ እኔም በምነግርህ  በአንድ ተራራ ላይ በዚያ እንደታዘዘው ልጁን ለመሥዋት አቀረበ። እንዲህ ያለ መታዘዝ ከልጅ የበለጠ የአምላክ ፍቅር እስከ ሞት ድረስ እንኳ እሺ ማለት ፍፁምነት ነው።

በእነዚህና በሌሎችም እግዚአብሔርንና  አብርሃምን ማመንና መታመንን፤ መታዘዝንና መባረክን፤ ፍፁም አብትነትንና  ልጅነትን አበክረን እንማራለን።

 ለዚህም ነው አባቶቻችን ሥላሴ የዓለም ሁሉ ፈጣሪ መጋቢ ሆነው ሳለ ለአብርሃም ብቻ አምላክ እንደሆኑ በሚመስል ቋንቋ ”የአብርሃሙ ሥላሴ“ በማለት የሚጠሯቸው። እውነትም ነው ይገባል! ሥላሴ የአንድነትና የሦስትነት፤ የአባትነትንና የልጅነትን፤የፈጣሪነትንና የፍጡርነትን፤ የአለቅነትንና የታዛዥነትን ጥልቅ ምስጢር እንድንረዳ የእግዚአብሔርን ድምፅ ብንሰማ ትዕዛዙን ብንቀበል እንደ  አብርሃም ልንባረክ ልንበዛ ልንከብር እንደምንችል ያሳየናል።

ምናልባትም አንዳንድ አላዋቂ የሆኑ ሰዎች ከመካከላቸው ይህ እኮ ምንም አይደለም አብርሃም ከኬጡራ ስድስት ከአጋር አንድ ልጅ አለው። ዘፍ 25፥1-17 ይስሐቅን ቢሠዋ ምንም አይደል ሊሉ ይችላሉ ነገር ግን እኒያ ልጆች አብርሃም በአህዛብነት ግብር ሣለ የወለዳቸው እግዚአብሔርን ሳያውቅና ሳያመልክ ያገኛቸው ናቸውና  ለበረከት ለርስት አልተመረጡም። ምሣሌነታቸው ባለፈውና በቀረው በባርነት ዘመን እንጂ በሚመጣውና በሚያከብረው በልጅነቱ ዘመን አይደለም። በመሆኑም

  • አብርሃም የእግዚአብሔር አብ፣
  • ይስሃቅ  የእግዚአብሔር ወልድ፣
  • እሳት የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምሳሌዎች
  • ሥላሴ የገቡበት የአብርሃም ድንኳን ”የእመቤታችን“ ምሣሌ ናት

ሥላሴ ወደ አብርሃም ድንኳን እንዲገቡ ሁሉ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያምም አብ ለአፅንኦ፣ መንፈስ ቅዱስ ለአፅንሆ፣ ወልድ በተለየ አካሉ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ለመዋሃዱ ምሣሌ ሲሆን አማናዊቷ የሥላሴ ማደርያ ድንኳን እመቤታችን ናት ሉቃ 1፥35

ሁሉም ምስጢር ከተፈፀመ በኋላ እግዚአብሔርም የሚያደርገውን ከአብርሃም እንደማይሰውር ገልፆለት የስዶምንና የገሞራን መጥፋት ነገረው። ኋላም ሦስት ሆነው ከገቡት ቤት አንዱ ቀርቶ ሁለቱ ወደ ሠዶም እንዳቀኑ ይነግረናል፤ ይህም ማለት አብና መንፈስ ቅዱስ ወደ ሰዶም ሲያቀኑ ወልድ በአብርሃም ድንኳን መቅረቱ ከአብርሃም ዘር ጌታ ሰው ለመሆን መፈለጉን ያመለክታል። ሮሜ 4፥16-18

ባጠቃላይ እንግዳን በመቀበል ምን ያህል ክብር እንደሚገኝ ከዚህ ምስጢር የተረዳን ሲሆን እግዚአብሔርም ሁል ጊዜ በኑሮአችን እንደማይለይ፣ የጎደለውን እንደሚሞላ፣ የረከሰውን እንደሚቀድስ ያወቅንበት ምስጢር ነው።

ቅዱስ ጳውሎስም ”እንግዶችን ለመቀበል ትጉ“ ሮሜ 12፥131 ብሎ እንዳስተማረን።

  እግዚአብሔርም የአብርሃምን እምነትና ፅናት መታዘዝና ፍቅር ተመልክቶ ”አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሴት አደረገ አየም ደስም አለው“ ዩሐ 8፥56 ብሎ  መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደመሠከረለት ሁሉ እኛም እንደ አብርሃም ማዳኑን አይተናልና የአብርሃምን መልካም ግብር ግብራችን አድርገን ከሥላሴ በረከት እንድንቀበል ያድርገን።

የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ በረከት በሁላችን አድሮ  ይኑር አሜን!

Share this post

የድርሻዎን እየተወጡ ነው?

ለአገልግሎታችን ቀጣይነት ቋሚ የሆነ ሕንጻ ለማግኘት የደብሩ ሕንጻ ኮሚቴ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ለቅድሚያ ክፍያ የሚያስፈልገን መጠን
£600,000
እስከ አሁን የተሰበሰበ
£450,000

የተጠቃሚ መግቢያ