የሰ/ት/ቤት ዓባላትሰንበት ት/ቤት መንፈሳዊ ወጣቶች በዕለተ ሰንበት፣ በዓበይት በዓላት፣ እና በወርኃዊ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያን እየተገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት እንዲሁም ምግባርን የሚያጠኑበት መንፈሳዊ ጉባኤ ነው። የለንደን ደ/ገነት ቅ/ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት በወቅቱ በነበሩት ሁለት ቀሳውስት ትጋት የተጀመረ ሲሆን በጊዜው የተሰበሰቡት ወጣቶች ዘወትር ቅዳሜ እየተገናኙ በሰቧሰቧቸው አባቶች መዝሙር በማጥናት እና በዕለተ ሰንበት በተቻላቸው መጠን መዝሙር በማቅረብ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

በወቅቱ ደብሩ የአንግሊካን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን (St. George Anglican Church) ሕንፃ ውስጥ የሚገለገል ስለነበረ ወጣቶች በዕለተ ሰንበት እየተገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት ለመማር አልቻሉም ነበር።

ነገር ግን የደብሩ አስተዳደር ከሕንጻው ባለቤቶች ጋር በመነጋገር አዳራሽ በማስፈቀዱ በየሳምንቱ የሰ/ት/ቤት ትምህርት መሰጠት ተጀመረ። በዚሁም አዳራሽ ከወጣቶቹ ባሻገር አዳጊ ህጻናትም መዝሙር እያጠኑ ያቀርቡ ነበር። ይህ አገልግሎት በእግዚአብሔር ፈቃድ ቀስ በቀስ እያደገ ሲሄድም የደብሩን የሰበካ ጉባኤ ምርጫ ተከትሎ በነሐሴ ወር 1998 ዓ.ም የሰንበት ት/ቤት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተቋቋመ። በቅዳሴ ጊዜ መዝሙር ከማቅረብ በተጨማሪ በየሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ልዩ ልዩ ተከታታይ ትምህርቶች /ኮርስ/፣ ስብከት እና ከጉባኤው በኋላ የመዝሙር ጥናት በማድረግ መንፈሳዊ አገልግሎቱ እንዲሰፋ ሆነ።

በመቀጠልም አገልግሎቱን በማጠናከር ወርኃዊ እና ዓመታዊ ጉባኤዎችን በማዘጋጀት ደብሩን እና ምእመናንን ማገልገሉን ቀጠለ። በተጨማሪም የደብሩ ዓመታዊ የስብከተ ወንጌል ጉባኤዎች በሚካሄዱባቸው ወቅቶች መንፈሳዊ ተውኔቶችን አዘጋጅቶ ማቅረብ ሰንበት ት/ቤቱ ሲሳተፍባቸው ከቆዩ አገልግሎቶች አንዱ ነው።

በበዓላት ላይም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ልዩ ልዩ ወረቦችንና መዝሙራትን በማጥናት እና በማቅረብ ከበረከቱ ተሳታፊ ሆኖአል።

ከሌሎች የሰንበት ት/ቤቶች ጋርም የአገልግሎት ልምድ ልውውጥ የሚያደርግ ሲሆን ከለንደን ውጪ የሚገኙ አጥቢያዎችን እና መንፈሳዊ ማኅበራትንም በማገልገል በኩል ዓባላቱ የቻሉትን ያህል ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

እንዲህ እንዲህ እያለ በእግዚአብሔር ቸርነት እያደገ በአሁኑ ወቅትም ፵፫ (43) አባላት ያሉት ሲሆን አባላቱም በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ተመድበው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ በየሳምንቱም ሆነ በየበዓላቱ ጎልቶ የሚታየው አገልግሎት መዝሙር ይሁን እንጂ ማንኛውም ወጣት ቀርቦ የቤተ ክርስቲያንን ልዩ ልዩ ትምህርቶች መካፈል፣ እንደየጸጋውም ማገልገል ይችላል።

እናንተ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንም ኑ! አብረን ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እንማር፣ እርሷንም እናገልግላት።

እዚህ ገጽ ላይ በመሄድ ቢጽፉልን እንመልስልዎታለን

የድርሻዎን እየተወጡ ነው?

ለአገልግሎታችን ቀጣይነት ቋሚ የሆነ ሕንጻ ለማግኘት የደብሩ ሕንጻ ኮሚቴ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ለቅድሚያ ክፍያ የሚያስፈልገን መጠን
£600,000
እስከ አሁን የተሰበሰበ
£450,000

የተጠቃሚ መግቢያ